አገልግሎቱ የሥነ-ምግባር ጥሰት በፈፀሙ 1 ሺህ...

image description
- Events ሰሞነኛ ዜናዎች    0

አገልግሎቱ የሥነ-ምግባር ጥሰት በፈፀሙ 1 ሺህ 77 አመራርና ሰራተኞች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገለፀ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተጠናቀቀው የ2016 በጀት አመት 1 ሺህ 77 አመራርና ሰራተኞች ላይ ከጹሑፍ ማስጠንቂያ እስከ ስንብት የሚደርስ አስተዳደርዊ እርምጃ መውሰዱን ገልጿል፡፡

እርምጃ ከተወሰደባቸው 1 ሺህ 77 አመራርና ሰራተኞች ውስጥ 88 ከአገልግሎት አሰጣጡ ጋር በተያያዘ የሥነ-ምግባር ጥሰት የፈፀሙ ሲሆኑ፣ 989 የሚሆኑት ደግሞ ተቋሙ ያስቀመጠውን የአሰራር ስርዓትና መመሪያዎች በመጣስ ወይም ባለማክበር ተጠያቂ የተደረጉ ናቸው።

ተቋሙ ባለፉት 12 ወራት ከአገልግሎት አሰጣጡ ጋር በተያያዘ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት 142 ጥቆማዎች ተቀብሎ ካጣራ በኋላ የሥነ-ምግባር ጥሰት በፈፀሙ 88 አመራርና ሰራተኞች ላይ የተለያዩ የዲሲፕሊን እርምጃዎችን የወሰደ ሲሆን፣ ቀሪ 54 የሚሆኑት ጉዳያቸው በሂደት ላይ ይገኛል፡፡

ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በባለድረሻ አካላት በቀረቡ ጥቆማዎች መሰረት ከታዩ ችግሮች መካከል በህገ-ወጥ መንገድ ቆጣሪ ማስገባት፣ ቆጣሪ ለማስገባት በሚደረገው ሂደት ጉቦ መጠየቅ፣ ደንበኛን በአግባቡ አለማስተናገድ፣ ያለበቂ ምክንያት ስራን ማዘግየትና ደንበኛን ማጉላላት፣ በአስቸኳይ ጥገና ስራ ደንበኞች ገንዘብ አዋጠው እንዲከፍሉ መጠየቅ፣ የቆጣሪ ማስገቢያ ክፍያ ገንዘብ ያለደረሰኝ መቀበልና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

ተቋሙ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃዎችን ከመውሰድ ባለፈ ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል የደንበኞች ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ቀላል እና ሚስጥራዊ የሆነ ዘመናዊ የጥቆማ ማቅረቢያ ስርዓቶችን ለመዘርጋት እየሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መረጃውን በፌስቡክ ገፁ አጋርቷል።

 


Comments

Nothing was found.

Leave Your Comments